እንኳን ወደ ሰቆጣ ከተማ በደህና መጡ

1.1 መገኛ

ሰቆጣ ከተማ የምትገኘዉ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል፣ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣  በዋግ ኸምራ ዞን፣ በሰሜን አበርገሌና ዝቋላ ወረዳ ከአዲስ አበባ በ565 ከባህርዳር 561 ኪሜ ርቀት ላይ ነው፡፡  አስትሮኖሚያዊ መገኛ ቦታዋ በ 4º53’’ሰሜን ላቲቲውድ እና 38º06’ ምስራቅ ሎንግቲውድ ላይ ነው፡፡

1.2 አመሠራረት

የሰቆጣ ከተማ የተቆረቆረችው በ410 ዓ.ም አካባቢ በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ ከተማዋ ከአክሱምና ሀረር ከተሞች ጋር በእድሜ እኩያ እንደሆነች አንዳንድ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ከተማዋ  በ5 ኛው ክ/ዘመን በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግስት የውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኝበት አካባቢ  ነበር የተቆረቆረችው፡፡ በሌላ ጊዜ ከውቅረ መስቀለ ክርስቶስ ተነስታ አሁን ካለችበት ቦታ በስተምዕራብ በሚገኘው ፈጥዝጊ በተባለ ከፍተኛ ቦታ ላይ ሆነ፡፡ ሆኖም ግን ቦታው የታሰበውን ያክል ምቾት ባለመፍጠሩ አሁን ወዳለበት ቦታ ሊዛወር ቻለ፡፡ ሰቆጣ  የሚለው ቃል ሸጉጣን ከሚለው የአገውኛ ቃል የመጣ ሲሆን የአማርኛ ትርጉሙም ሸጉጠው ማለት ነው፡፡ ሰቆጣ በክልሉ ከሚገኙ የሪፎርም  ከተሞች አንድዋ ስትሆን የከተማ አስተዳደር፣ ማዘጋጃ ቤትና 3  ቀበሌዎች  አሷት፡፡ በ2000 ዓ.ም የተዘጋጀ የዕድገት ፕላን አላት፡፡